በሀገሪቱ ከሚገኙ ቅርሶች እድሳት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የተጠናከረ ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አሰታውቋል። የባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ ዘለቀ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸውን ቅርሶች የቀደመ ይዘታቸው ሳይቀየር ለማደስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም የጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግስትና የጢያ ትክል ድንጋይ እድሳት በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት። በሌላ በኩል የፋሲል አብያተ መንግስታትን እድሳት ስራ ማከናወን የሚያስችል የቅድመ ጥገና ጥናት ለመጀመር ዝግጅት እተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን በዘላቂነት ለማደስም ከፈረንሳይ መንግስት ጋር እየተሰራ መሆኑም አስረድተዋል። ለእደሳቱ ስራ የሚደረገው ጥናት መጀመሩን የገለጹት አቶ ሃይሉ ፥ ይህም እስከ ታህሳስ 2013 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ አንስተዋል። የጥናት ውጤቱን ተከትሎም ተግባራዊ የጥገና ስራው ይጀመራል ብለዋል።
Source: Fana Broadcasting Corporate