ምክንያቱን ባላውቅም ብዙ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ከማየትና ከመጎብኘት ይልቅ ከቻሉ ወደ ውጭ መጓዝን ይወዳሉ። ለስደትም ቢሆን። የጉዞ መዳረሻዎችም ሳይቀሩ ከራሳቸው ዜጎች ይልቅ የውጭ ጎብኝዎችን ለማስተናገድ የተመቻቹ ናቸው። ከአማርኛ ከኦሮምኛ ከትግርኛ ወይም ከሌሎች የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ይልቅ ብዙም ባልቀና እንግሊዘኛ ታሪክን ማስረዳት ይቀላቸዋል። ይህ የቅርብ ማለትም የሶስትና የአራት ዓመት ክስተት ብቻ አይደለም። በእርግጥ በቅርብ ጊዜ አገራችን ቀበሌ አቋርጦ ለመጓዝ አይደለም ለኗሪዎቿም ፈታኝ ሆናለች። በአውቶቡስ ስትጓዙ ኪሳችሁን ለመዳበስ አለበለዚያም ማደሪያ አልጋ እንድትይዙ ሊያግባባችሁ ካልሆነ በቀር የአካባቢውን ታሪክ ሊያስረዳችሁ የሚሞክር እምብዛም ነው። ድሮም ቢሆን።
ኢትዮጵያውያን አብሮ ለመኖር አገራቸውን በልኳ ማወቅ የግድ የሚላቸው ወቅት ላይ ናቸው። ምንአልባትም አሁን ላይ ያለው ግርግር ዜጎች አገራቸውን በልኳ ካለማወቃቸው የተነሳ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መሰረቱ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው በገጠሩ የሚኖረው ኩሩው ገበሬና አርብቶ አደር ማህበረሰብ ነው። ይህ የሀገሪቱ መሰረት የሆነው የገጠሩ ማህበረሰብ ደግሞ እምቅ የሆኑ ማህበራዊ ሀይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ነው። ያውም ጠንካራ የሆኑ። ለዛም ነበር ምንም እንኳን አዲስ አበባ ላይ ጫጫታ ቢበዛም ሀገሪቱ ነቀነቅ ሳትል የኖረችው።
Read More: #10 Unique Attributes You Need to Know As You Travel to Ethiopia for the First Time
ይሁን እንጂ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የህዝባችን የእድሜ ስብጥር( ዲሞግራፊ) በእጅጉ እየተቀየረ እየሄደ ነው። ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የወጣቶች ሀገር እንደምትሆን እየተተነበየ ነው። ይህ ጥሩ እድል ቢሆንም ጥሩ ያልሆነ ነገር ይዞ መምጣቱም የማይቀር ነው። በቅጡ ካልተዘጋጀን በስተቀር። የትምህርት ጥራት ጉድለት ተጨምሮበት ወጣቱ ትውልድ ጠንካራ የነበረውን የአባቶቹን እሴቶች ይዞ ለመቀጠል ሲቸገር እየታዘብን ነው። በእጅጉ መላላት ይታይበታል። ውጭ ከሚያድገውና የእኛን የኑሮ ዘይቤ በሶሻል ሚዲያ ብቻ ከሚያውቀውማ ፈጣሪ ይጠብቅን።
ሌሎች የመንግስት ፖሊሲዎች እንደተጠበቁ ሆነው ወጣቱ ሀገሩን በሚገባ እንዲያውቅ መደረግ ይኖርበታል። የሀገር ውሰጥ ጉብኝትን በማበረታታት። አጠቃላይ የቱሪዝም ሴክተሩን ለማበረታታት የሚደረጉ ድጋፎችና ጥረቶች ሁሉ የሀገር ውስጥ ጉዞንና ጉብኝትን እንዲያካትቱ ቢደረግ ሴክተሩን በቶሎ ወደነበረበት ለመመለስ ይረዳል። አለም አቀፍ ትንበያዎች እንደሚያሳዩት ሀገራት ከኮቪዲ በኋላ የሀገር ውስጥ ጉብኝትን ማነሳሳት እንደቅድሚያ ስራ ወስደው በመስራት ላይ ይገኛሉ። ተጓዞች ደህንነት እንዲሰማቸው ለማድረግ። ኢትዮጵያም በዚሁ መንገድ ብትሄድ ታተርፋለች። ይህ ሲሆን ቱሪዝሙን ከማነቃቃት ባሻገር ዜጎች ሀገራቸውንና ማንነታቸውን ይረዳሉ። ሀገራቸውን በቅጡ ሳይረዱ ፖለቲካ ውስጥ የገቡ ብዙ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ላይ እጅግ የበዛ ጉዳት አድርሰዋል። ወደፊትም ያደርሳሉ። እንዲያውቁ ካልታገዙ።
Read More: The 5 Key Highlights You Need to Know About GERD as You Travel to Ethiopia
እውነት ለመናገር ዩኒቨርሲቲ በቆየሁባችው ጥቂት ዓመታት ውስጥ የሸመትኩትና እስካሁንም ድረስ አብሮኝ ያለው ስለሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቼና እህቶቼ ማንነት የተማርኩት ቁም ነገር ነው። ከሰርተፊኬቱ በተጨማሪ። ሌላውንማ ሂወት ነች ያስተማረችኝ። ድሮ ዩኒቨሲቲዎች የሀገሪቱ ወጣቶች የእርስ በእርስ መተዋወቂያና መግባቢያ ነበሩ። በቅርቡ የብሄር ጦር ሜዳ ከመሆናቸው በፊት። ይሄ መቀየር አለበት። አያዋጣም። እንደመነሻ ያህል በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ከትምህርትና ከስራ ገበታ ውጭ ሆኖ የሚጠባበቅውን ወጣት ሀይል በኢትዮጵያ እያዞሩ ስለ ሀገሩ ማስተማር ማሰቡ አይከፋም። ብሄራዊ መልክ ይዞም ቢሆን። ካለበለዚያ ወደለመደው የብሄር ጦርነቱ በትጋት እንደሚመለስ መገመት አያዳግትም።
ብዙ ወጣቶች ሀገራቸውን በብዥታ ነው የሚያውቋት። አሁን አሁን ሌላው ሰው ነገር ሲሸርብ የሚያድር የሚመስለው ሌላ ቋንቋ ሲሰማ ጆሮውን የሚቆረቁረውና ሚስጥር ብቻ የሚወራ የሚመስለው ፈታ ብሎ የሚያወያራ ሲሰማ የሚጠራጠር ኢትዮጵያዊ በበዛበት ሁኔታ መፍትሄው መቀራረብና መተዋወቅ ነው።እንደማንተዋወቅ ብዙ ማሳያዎች አሉ። እንዲያውም የማንተዋወቀው ሳይበዛ አይቀርም። ቢያንስ በደንብ ከተዋወቅን በኋላ ለመጣላትም ምክንያት ይኖራል።
Read More: Gursha, Ethiopians Message of Kindness and Love
በአንድ ወቅት ቴሌቪዥን ላይ ያዳመጥኩት አንድ የሃገራችን ሰው ባህር ዳር ለትልቅ ስብሰባ ተገኝቶ በጋዜጠኛው ከስብሰባው ምን አዲስ ነገር እንደተማረ ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ‘ እኔን የገረመኝ የአካባቢው ሰው በባዶ እግሩ ማለትም ያለጫማ መሄዱ ነው’ ብሎ የመለሰው መልስ ነበር። በቅርቡ ደግሞ በተመሳሳይ አንድ የፖለቲካ መሪ የሆነ ሰው በአንዱ የሀገራችን ክፍል ከጉብኝት ሲመለስ ህዝቡ በድህነት እንደሚኖርና ድሮ ከሚሰማው በፍጹም እንደተለየበት በቴሌቪዥን መስኮት ሲናገር ሰማሁትና ገረመኝ ። ሶሻል ሚዲያ ላይ የሚያውቃትን ኢትዮጵያ ይዞ ለምርጫ እንደሚቀርብ ተሰማኝ። እነዚሀ ያነሳሁላችሁ ሰዎች የፖለቲካና የሀገር መሪዎች ናቸው። ወጣቱማ እድሉንም አልፈጠረም አላገኘምም። በግማሽ ቀንና በአንድ የጉዞ ቲኬት የምንረዳቸውን እውነቶች ልክ እንደ ሌላ ሀገር ክስተት እናወራቸዋለን።ለብሄር ብሄረሰቦች በዓል እንኳን በየዓመቱ የሚሄዱት ተመሳሳይ ሰዎች ናቸው። ቢያንስ ትንሾች እንኳን በየዓመቱ እንዳይተዋወቁ።
Read More: Ethiopian Tourism Poised to Maneuver Post COVID-19
ብዙ የሀገራችን ወጣቶች ሌሎች ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሲሉ ከእነሱ በተለየ መልኩ ከኢትዮጵያ ተጠቃሚ ስለሆኑ ይመስለዋል። ኢትዮጵያ የሚሉም ቢሆኑ ሌሎችን ቀርቦ ከማስረዳትና ከማንቃት ይልቅ መኩራራት ይቀለዋል። አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስላልክ ብቻ አሀዳዊ ወይንም ደፍጣጭ ይሉህና እራሳቸውን የብሄር ብሄረሰብ ጠበቃ አድርገው ደብል ስታንዳርድ ይመቱብሃል። ብዙ ጊዜ የምንዘነጋው ጉዳይ ቢኖር በሃገራችን ጉዳይ ላይ ሁላችንም እኩል ወሳኝ መሆናችንን ነው።
እናም እኔም እልሀለሁ
ግቤን ተሻግረህ ባሮን ካላየህ
አርባ ምንጭን አልፈህ ኮንሶን ካልጎበኘህ
አዋሽን ተሻግረህ ምስራቆችን ካልዘየርህ
ደዴሳን ዘለህ የምዕራብ ተራሮችና ጫካዎች ካላስጎመጁህ
የባሌ ተራሮችን እያየህ ነገሌ ቦረና አድረህ ሻኪሶ ካልዘለቅህ
አድባሩን አባይን ተሻግረህ ጣናን ካልጎበኘህ ፋሲል ካላስደነቀህ
ወሎ ገራገሩን አቋርጠህ ላልይበላን ካልጎበኘህ
አክሱም ተገኝተህ ታሪክህን ካልመረመርህ አድዋን ካልሰነቅህ
እንዴትስ ስለ ኢትዮጵያ ትመሰክራለህ።
መማርና መመራመር ወሳኝ ጉዳይ ነው። ለማወቅ። በአካል መገኝትና መጎብኘት ግን ሁሉን ነገር ያቀልልሃል። በቦታው ስትገኝ በሩቅ የሰማኸው ብዥታህ በአካል ይገለጽልሃል። እውነት ለመናገር የትኛውም ታሪካዊ ትርክታችን ቢሆን ከአድሏዊነት የጸዳ አይመስለኝም። የታሪክ ተመራማሪ አይደለሁም። የዛሬን ውዥንብር እየኖርኩ የትናንትን መገመት ግን እችላለሁ። ስንቶቻችን ነን ምስራቆች ግራኝ አህመድን ልክ እንደቴወድሮስ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ግዛት ሲያስፋፋ እንደነበር እንደሚያምኑ የምንቀበለው። እረ እንዲያውም የምናውቀው።
በአንድ ወቅት አንድ ጓደኛየ የነገረኝን አልረሳውም። ጓደኛየ የክፍለ ሀገር ልጅ ነው። የእሱ ጓደኛ ደግሞ ከአዲስ አበባ ነው። በአንድ ወቅት ለስራ ጉዳይ ይመስለኛል ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር በመጓዝ ላይ ሳሉ ልክ አባይ በረሃን እንደተሻገሩ የአዲስ አበባው ጓደኛው በመገረም እንዲህ አለው። እንደነገረኝ። እኛ እኮ( አዲስ አበቤዎች ማለቱ ነው) ታዝለን ነው የምንሞተው። አዲስ አበባ ተወልዶ አዲስ አበባ ተምሮ አዲስ አበባ ተኑሮ አዲስ አበባ እንደማለፍ ማለቱ ነበር። ገላንና ቡራዩ እንኳን ሳይደርሱ እንደማለት ነው። ይህን እንደምሳሌ አነሳሁት እንጂ የትም ቢሆን በቋንቋ ከሚመሳሰለውና ከቀበሌው ከወጣው ማንነቱ ጋር ብቻ ታዝሎ የሚያልፈውን ቤት ይቁጠረው። በአካባቢው በትምህርት ቤት በስራ ቦታ እንዲሁም በመዝናኛ ቤት ጭምር ከሚመሳሰለው ጋር ብቻ ከተጓዘ እንዴትስ ስለጎረቤቶቹ እንዲያውቅ እንጠብቃለን።
ዓለም ከኮቪዲ ስታገግም የቱሪዝም ንግድ ውድድሩ ከአሁን በፊት ከተለመደው በተለየ መልኩ ጠንካራ እንደሚሆን ይጠበቃል። ሀገራችን ኢትዮጵያ በቂና ተውዳዳሪ የሆኑ የቱሪዝም ሀብቶች አሏት። ተጨማሪ መስህቦችም በመምጣት ላይ ናቸው። በዋናነት የሚጎድለውና መሰራት የሚኖርባቸው የአጠቃላይ ሀዝቡ የቱሪዝም ንቃት ፈጣን የሆነ የመንግስት አመራርና የፖሊሲ ድጋፍ እንዲሁም የሁሉም ባለጉዳዮች በተለይም ደግሞ የትራንስፖርት ዘርፉ የአስጎብኝ ድርጅቶችና የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚፈለገውን ዝግጅት ማድረግና ተቅናጅቶ መንቅሳቅስ ነው። በተለመደው መንገድ መጠበቅ ቱሪዝሙን የትም እንደማያደርስው ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል። ከመንግስት ባሻገር ሁሉም አካላት ሴክተሩ አሁን ላይ ያለበትን ደረጃና የሚጠብቀውን ፈተና በሚገባ ተረድተው መንቀሳቀስ የግድ ይላል።
የ10 ዓመቱ የቱሪዝም መሪ ዕቅድም ቢሆን የሀገር ውስጥ ጉዞንና ጉብኝትን ጭምር የማሳደግ እንዲሁም የአገልግሎት ጥራቱ ሁሌም የሚረጋገጥበትን መንገድ በግልጽ ማስቅመጥና ማስጠበቅ ይጠበቅበታል። ቴክኖሎጂን እንደ ዋነኛ መሳሪያ በመጠቀም ጭምር። ይህ ሲሆን የቱሪዝም ሀብቱ የሚጠበቅበትን ድርሻ ለኢኮኖሚው ሲያበረክት ዜጎች ደግሞ ሀገራቸውን በልኳ ይገነዘቧታል። ዜጎች ስለሃገራቸው የበለጠ ባወቁ ቁጥር አጠቃላይ የቱሪዝም ልማቱን ያግዙታል።
እናም በኢትዮጵያ እንጓዝ ስለኢትዮጵያ እንማር እኛም እንተዋወቅ።
ማሳሰቢያ፡ የዚህ ጽሁፍ ሙሉ ሃፊነት የጸሀፊው እንደሆነ ለማስገንዘብ እንወዳለን። አፍሮ ኤክስፒሪያንስ ለጋራ ስኬት የድርሻውን ይወጣል። ጦማራችንን ተከተሉ።
እራሳችሁን ቤተሰቦቻችሁንና ወዳጆቻችሁን ሁሉ እጃችሁን ቶሎቶሎ በመታጠብ እርቀታችሁን በመጠበቅ ተገቢውን የፊት መሸፈኛ በማድረግ ከተቻለም የበሸታ መከላከል አቅምን የሚገነቡ ምግቦችን በመመገብ ከግዜው ወረርሽኝ መጠበቃችሁን አትዘንጉ።
.